በግርማቸው ከበደ

አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2009 ዓ.ም – ከአንድ ሳምንት በኋላ በእንግሊዝ ለንደን የሚካሄደውን 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ምክንያት በማድረግ በወቅታዊ የአትሌቲክስ ጉዳዮች እና የዘገባ ጥራት ላይ ያተኮረው፤ በኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስፖንሰር በሆነው ሶፊ ማልት ትብብር የተዘጋጀው የአንድ ቀን የማነቃቂያ ስልጠና በስኬት ተጠናቋል፡፡

ከ70 በላይ የሚሆኑ የስፖርት ጋዜጠኞች በተሳተፉበት ስልጠና የመክፈቻ ንግግር ያደረገው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዮናስ ተሾመ ‹‹ ስልጠናው በሀገራችን ሚዲያዎች የአትሌቲክስ ዘገባ ጥራትን ከፍ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው›› ብሏል፡፡ በሄይኒከን ኢትዮጵያ የሶፊ ማልት የብራንድ ማናጀር የሆኑት ወ/ሪት ራህዋ ገ/መስቀል በበኩላቸው ሶፊ ማልት የኮርፖሬት ማህበረሰባዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጋር መስራቱ እንዳስደሰታቸውና ወደፊትም ይህ ግንኙነት እንዲቀጥል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግዳነት የተገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገ/ስላሴ ለስፖርት ጋዜጠኞች ባስተላለፈው መልዕክት የሚዲያውን አስፈላጊነት እንደሚረዳ እና እንደሚያደንቅ ከገለፀ በኋላ ‹‹አትሌቶቹም ሆነ ስፖርቱ በአጠቃላይ ያለሚዲያው የትም አይደርሱም›› የሚል አስተያየትን  የሰጠ ሲሆን በስልጠናው ተሳታፊዎች ለቀረቡለት ጥያቄዎችም ማብራሪያዎችን  ሰጥቷል፡፡

በስልጠናው ላይ የመወያያ የመነሻ ሃሳብ ያቀረበው የማህበሩ አባል ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል ለአትሌቲከስ ዘገባ ጥራት እንቅፋት ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች አንስቷል፡፡ የአትሌቶቻችን ለሚዲያው ቅርብ አለመሆን፣ የጋዜጠኞች ከውጤት ዜና ባለፈ ያሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አለማድረግ እና በዘገባዎች ላይ የሚንፀባረቅ ስሜታዊነት በምክንያት ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት የአትሌቲክስ ዘገባ ጥራትን ከፍ ለማድረግ እንደሚያስችሉም ተናግሯል፡፡ የስልጠናው ተሳታፊዎችም ለዘገባዎች መሻሻል መደረግ አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡

 

በኢንተርኮንቲነንታል አዲስ ሆቴል በተካሄደው የማነቃቂያ ስልጠና በፓና ፕሮሞሽን የተሰራው የማህበሩ አዲስ ድረ-ገፅም  ተመርቋል፡፡

Please follow and like us:

One Response to የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ከሶፊ ማልት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ስልጠና ተካሄደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *