በ አስፋው ስለሽ

የኮፓ ኮካኮላ ትምህርት ቤቶች ማጠቃለያ ውድድር በጅግጅጋ ከተማ እየተከናወነ ይገኛል፡ ዘጠኝ ክልሎችና ሁለት የከተማ መስተዳደሮች እየተሳተፉበት ነው፡፡

ከሻምፒዮናው ጥሩ ብቃት ያሳዩ 79 ታዳጊዎች ወደ ኢትዮጵያ እና ጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች ስፖርት ማሰልጠኛ ማእከላት ለተሻለ ስልጠና ይገባሉ፡፡

የውድድሩ ተሳታፊወች በከፊል በአዲሱ የጅግጅጋ ስታዲየም፡፡ Photo by: Haileegziabher Adhanom

ቅዳሜ በተጀመረውና እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ 11 የሴትና 11 የወንድ እግር ኳስ ቡድኖች በሚሳተፉበት ሻምፒዮና አዘጋጁ ኢትዮ ሱማሌ ክልል ያልተጠበቀ ድል አስመዝግቧል፡፡ ጠንካራውን ኦሮምያን ከጨዋታ ብልጫ ጋር 6 ለ 1 አሸንፎታል፡፡

ተስፋ ሰጪ ታዳጊዎች በታዩበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለተመልካች ሳቢ የሆነ እግር ኳስ ታይቶበታል፡፡ 10 ሰዓት ላይ በተደረገ ሌላ ጨዋታ ደቡብና ጋምቤላ ክልሎች 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች በሚሳተፉበት የኮፓ ኮካኮላ ሻምፒዮና የሴት እግር ኳስ ቡድኖችም ጨዋታቸውን አድርገዋል የመክፈቻው እለት በተደረገ ጨዋታ ደቡብ ድሬደዋን 4 ለ 0 አሸንፏል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የኮካኮላ ካምፓኒ በጋራ ለ3ኛ ግዜ እያከናወኑት በሚገኘው ውድድር በችሎታቸው ልቀው የሚገኙ ተጫዋቾች ወደ ታዳጊ ወጣቶች ማሰልጠኛ ይገባሉ ተብሏል፡፡

በቅድሚያ በሃገሪቱ ላይ ከሚገኙ 2ሺ ትምህርት ቤቶች በተገኙ 36,000 ታዳጊዎች መካከል የማጣሪያ ውድድር የተደረገ ሲሆን ይህ በጅግጅጋ ከተማ ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ውድድር የማጠቃለያ እንደሆነ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በየዓመቱ የሚታዩትን ምርጥ ምርጥ ክህሎት ያላቸው ታዳጊዎችን አቅም ለመጠቀም ክለቦች አይናቸውን ወደ እነዚህ አይነት ውድድሮች ላይ ሊያሳርፉ ይገባል ፡ ፌዴሬሽኑም ክለቦች በታዳጊዎች ላይ እንዲሰሩ የሚያስገድድ ህግ ለማውጣት በዝግጅት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኮካኮላ ካምፓኒ የምስራቅ አፍሪካ ዞን ማናጀር ወ/ት ትዕግስት ጌቱ በበኩላቸው ካምፓኒው የኢትዮጵያ ታዳጊዎች የኳስ ክህሎታቸውን የሚያሳዩበትን መድረክ በማመቻቸቱ በኩል ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮካኮላ የተለየ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች እስከመጨረሻው ድረስ በመከታተል ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ ጥረት ያደርጋልም ብለዋል፡፡

የኮፓ ኮካኮላ የታዳጊዎች ውድድር በአለም ላይ ትላልቅ ተጫዋቾች የተገኙበት ሲሆን ከአፍሪካ ኬንያዊው ቪክቶር ዋኒያማ ከላቲን አሜሪካ ደግሞ ጥበበኛው ብራዚላዊ ሮናልዲኒሆ ጎቾ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *