በ  ቆንጂት ተሾመ 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ውስጥ በአመራርነት ተወዳድራ ቦታ ማግኘት ችላለች። የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው ጋዜጠኛ ዮናስ ተሾመ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ ኢትዮጵያ የመሪነት ቦታ አግኝታለች።

የአለምአቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አካል የሆነው የአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ኮንግረስ በኬንያ ናይሮቢ ለሶስት ቀናት ተካሒዷል። ስብሰባው የኬንያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንትና በቀድሞ አትሌት ፖል ቴርጋት የመክፈቻ ንግግር የተጀመረ ሲሆን፤ የአለምአቀፉ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ጣሊያናዊው ጂያን ሜርሎና ምክትል ፕሬዝዳንቷ ኬንያዊቷ ኤቭሊን ዋታ የምርጫ ሒደቱን ተከታትለዋል።

በመጀመሪያው ዙር ክሪስ ሙባሲ 18፤ ሙፍቲ ሙሀመድ 15 ድምጽ አግኝተው በቀጥታ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታን ማግኘት ችለዋል። የኢትዮጵያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና የጊኒ ተወካዮች እኩል 12 ድምጽ በማግኘታቸው ሁለቱን እጩዎች ለመምረጥ በተደረገው ሁለተኛ ዙር ምርጫ 18 እና 13 ድምጽ በማግኘት የኢትዮጵያና ጊኒ ተወካዮች አሸንፈዋል። የዲሞክራቲክ ኮንጎው ተወካይ ካቡሎ ምዋና ካቡሎ አነስተኛ የሆነውን 12 ድምጽ በማግኘቱ አመራሩን ሳይካተት ቀርቷል።

ማህበሩን አራት ምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ተመራጮችም ኢትዮጵያዊው ዮናስ ተሾመ፤ ኬንያዊው ክሪስ ሙባሲ፤ እና የጊኒው አማዱ ዲዩልዴ ዲያሎ፤ እንዲሁም ሱዳናዊው፤ ሙፍቲ መሀመድ ሰኢድ ናቸው።

ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያለተቀናቃኝ ብቸኛው እጩ ሆኖ የቀረበው ናይጄሪያዊው ሚሼል ኦቢ በድጋሚ ሊመረጥ ችሏል። የሞሮኮው ሙራድ ሙታኡኪ በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲመረጥ፤ በዋና ጸሐፊነት ደግሞ ጋናዊው ሚልም ዶድዚ ኢዛህ አሸንፏል። በምክትል ዋና ጸሐፊነት ቦታ አንቶኒዮ ጎንቻለቭስ ፌሬራ ከአንጎላ እና መሀመድ ሲሊማኔ ከኒጀር ተመርጠዋል። ለአቃቤ ንዋይ ቦታ ያለተፎካካሪ የቀረበው የቤኒኑ ተወካይ ሒሳብ ፌሊክስ ሶሆንዴ ፔፔሪፕ ቦታውን መያዝ ችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ኡመር ባባ ትራኦሬ ማሊ እና ብዱላዬ ቲያም ሴኔጋል መካተታቸው ታውቋል።

በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ተጨማሪ አራት ተወካዮችን ለማካተት ክፍት ቦታ እንዲኖር የተደረገ ሲሆን፤ ከአራት ወራት በኋላ በቱርክ በሚካሔደው የአለምአቀፉ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ኮንግረስ ስብሰባ ይመረጣሉ ተብሏል።

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *