በ ኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም

የአለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) በየአራት አመቱ በሚያከናውነው የአለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ላይ አሸናፊ ለሆኑ ብሄራዊ ቡድኖች በሽልማት መልክ የሚሰጠው ዋንጫ (The FIFA World Cup Trophy) በመላው አለም ጉዞ እያደረገ ይገኛል፡፡


ይህ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጥበቃ የሚታጀበው የአለም ዋንጫ ሽልማት፤ ከ2018ቱ የሩሲያ አለም ዋንጫ አስቀድሞ በመላው አለም በተመረጡ 51 ሃገራት እና 91 ከተሞች ጉዞውን የሚያደርግ ሲሆን ሀገራችን ኢትየጵያም ዋንጫው እንዲጎበኛቸው ከተመረጡ 10 የአፍሪካ ሀገራት አንዷ በመሆኗ የካቲት 17 እና 18/ 2010 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በተላያዩ መሰናዶዎች የሚቆይ ይሆናል፡፡

የፊፋ የአለም ዋንጫ በአ.አ

ዋንጫው ቅዳሜ የካቲት 17/2010 ዓ.ም ከሱዳን ካርቱም ተነስቶ አዲስ አበባ ቦሌ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ ሲገባ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁኔዲ ባሻ እንዲሁም ሌሎች የስፖርቱ ቤተሰቦች፣ የመንግስት እና የኮካ ኮላ ኩባንያ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ደማቅ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን፤ በእለቱም በብሔራዊ ቤተ መንግስት በተደረገ የምሳ ግብዣ በኢፌዴሪ መንግስት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ይፋዊ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በብሔራዊ ቤተ መንግስት በተካሄደው የአቀባበል ስነ ስርዓት ላይ የክብር እንግዳ የነበሩት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የዓለም ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በወጣቶቻችን ላይ መነሳሳት በመፍጠር ለእግር ኳሱ እድገት ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የአለም ዋንጫውን ከፊፋ ጋር በመተባበር ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው ኮካ ኮላ ካምፓኒ የኢትዮጵያ እና ምስራቅ አፍሪካ ብራንድ ማኔጀር ወ/ሪት ትእግስት ጌቱ በበኩላቸው ‹‹ ኮካ ኮላ እግር ኳስን በፍቅር ለሚወዱ ኢትዮጰያውያን ብዙዎች የሚመኙትን የአለም ዋንጫ በቅርበት እንዲመለከቱት እና እነዲነሳሱ ከማድረጉ በተጨማሪ በየአመቱ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በሚያከናውነው የወጣቶች ሀገር አቀፍ እግር ኳስ ውድደር ላይ ጠንክሮ በመስራት ዋንጫውን አሸንፈው የሚመጡ ታዳጊዎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እንደሚወጣ መናገር እወዳለሁ›› ብለዋል፡፡

የፊፋ አለም ዋንጫ የኢትዮጰያ ጉብኝት የመጨረሻ መርሀ ግብሩ የሚሆነው በዛሬው እለት በሂልተን አዲስ አበባ ሆቴል እተከናወነ የሚገኘው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚጋብዘው የፎቶ መነሳት መርሀ ግብር ሲሆን በነገው እለት ወደ ቀጣዩ መዳረሻው ጎረቤት ሀገር ኬንያ የሚያመራ ይሆናል፡፡

 

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *