Monthly Archives: April 2018

በኦምና ታደለ

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር፣ ከአለምአቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በትብብር ያዘጋጀው ስልጠና በሳምንቱ መጨረሻ ሚያዚያ 6 እና 7/2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ አዘማን ሆቴል ተካሂዷል፡፡ ስልጠናው በዋናነት በዘመናዊ የስፖርት ጋዜጠኛነት እና ፈተናዎቹ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡


በአዘማን ሆቴል የተካሄደውን ስልጠና የሰጡት የአለምአቀፉ የስፖርት ጋዜጨኞች ማህበር አስተማሪ እና ከ25 ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኛነት ያሳለፉት ጣሊያናዊው ሪካርዶ ሮማኒ ሲሆኑ፡ ስልጠናው ጋዜጠኞች በዘመናዊው የሚዲያ አለም ፈጣን እና ትክክለኛ መረጃዎችን በማመጣጠን እንዴት ማቅረብ እንደሚችሉ ተሞክሯቸውን በመጨመር ያካፈሉበት ነበር፡፡

በስልጠናው በተጨማሪም ጋዜጠኞች ለዜናዎች እና ትንታኔዎች በቂ ዝግጅት አድርጎ አግባብ የሆነ እና በፍሬ ነገር የተሞላ ዘገባ ማድረስ እንደሚቻል እንዲሁም በአንድ ግዜ ከአንድ በላይ ሙያዊ ክንዋኔዎችን እየሰሩ በዘመናዊው የሚዲያ አለም መላመድ እንደሚቻል ለማሳየት የተሞከረበት ስልጠና ለኢትዮጵያዊያን የስፖርት ጋዜጠኞች ተሰጥቷል፡፡ ሮማኒ በስልጠናው ላይ ዘመናዊ የስፖርት ጋዜጠኞች ከመፃፍ በዘለለ ፎቶዎች አና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ማንሳት እና ማረም ከጋዜጠኞች ዘመኑ የሚጠይቀው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የስፖርት ጋዜጠኝነት እና ስነ-ምግባር ሌላው በስልጠናው ላይ አፅኖት ተሰጥቶት ሰፊ ውይይት የተደረገበት ጉዳይ ነበር ፡፡ ስፖንሰርሺፕ፣ የፋይናንስ አቅም እና ፖለቲካ በብዛት ተፅዕኖ በሚያሳድሩበት የሚዲያ አለም ላይ የስፖርት ጋዜጠኞች ነፃ ለመሆን የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ላይ ስልጣና ተሰጥቷል፡፡
የአለምአቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር መሰል ስልጠና በኢትዮጵያ ሲሰጥ ይህ ለመጀመሪያ ሲሆን ፡ ቀጣይነት እንዲኖረውም በስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ ጋዜጠኞች ሀሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

ስልጠናውን ከባህርዳር እና ሀዋሳ የመጡትን ጨምሮ በአጠቃላይ 66 የስፖርት ጋዜጠኞች የተከታተሉት ሲሆን፡ በአግባቡ ላጠናቀቁ 54 ጋዜጠኞች ደግሞ የአለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አለምአቀፍ ይዘት ያለው የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርም ለዚህ ስልጠና መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉትን አለምአቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርን፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን እና አዘማን ሆቴልን በማህበሩ አባላት ስም በማመስገን መርሀግብሩ ተጠናቋል፡፡

Please follow and like us: