በ ግርማቸው ከበደ

የሁሉም አይኖች ላይ ጉጉት አለ፡፡ እየተያዩ ፈገግ ይላሉ፡፡ በዚህ ሳምንት የሚነግሱበትን ትራክ በእግሮቻቸው ነካ…ወጋ…እያደረጉ እንደገና ይስቃሉ፡፡ በእግሮቻቸው እና በትራኩ ንኪኪ የሚፈጠረው “ድምድምታን” እንደ ማጀቢያ ሙዚቃ እየተጠቀሙ ስለምቾቹ በደስታ ይወያያሉ፡፡

ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ሊሰሩ ታምፔሬ ስታድየም ተገኝተዋል፡፡ ይህ የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ውድድር ነው፡፡ አትሌቶቹ ወደ “ዋናው” ብሔራዊ ቡድን የሚሸጋገሩበት፡ “ሲኒየር” ከመሆናቸው በፊት ለዓለም አትሌቲክስ ራሳቸውን የሚያሳዩበት መድረክ ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በወጣቶች ሻምፒዮና ራሱን ለዓለም ያስተዋወቀውን አለቃቸው ኃይሌ ገ/ስላሴን መመልከት ይበቃቸዋል፡፡

ይህ ግን አይጠፋባቸውም፡፡ ታምፐሬ የተገኙት ቀጣዩን ገፅ ለመግለጥ ነው፡፡ የታምፐሬ ስታድየምን ትራክ በእግራቸው እየፈተሹ የሚሳሳቁትም ለዛ ይሆናል፡፡ በድንገት ግን “ልምምዱን ሜዳ ላይ እንስራ!” የሚል ድምፅ ተሰማ፡፡ “አዎ…እሺ!”…

የፓርክ ልምምድ

ከስታድየም ወጥተው ሜዳ ፈለጉ፡፡ ደግነቱ ከስታድየሙ ውጭ ሜዳ አልጠፋም፡፡ በፕሃያርቪ ሃይቅ ዳር ባለ ጎዳና ሰውነታቸውን ማፍታታት ጀመሩ፡፡ የፓርኩ የጤና ሯጮች የኢትዮጵያ አትሌቶች በእነርሱ ጎዳና እያሟሟቁ እንደሆነ አውቀዋል፡፡ በበረራ የደከመ ሰውነትን ለማፍታት የተጀመረው ሩጫ ወደ ጠንካራ ልምምድ ተቀየረ፡፡ አሰልጣኞቹ “በቃችሁ!” ቢሉም ለጥቂት ደቂቃዎች ሰሚ አላገኙም ነበር፡፡ ወጣቶቹ በስሜት ተሞልተው ይለማመዳሉ፡፡ በታምፔሬ ለመንገስ ይተጋሉ፡፡

“አዲስ ትውልድ”

የ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ “ልጆቹ ጥሩ ስሜት ላይ ናቸው” ይላሉ፡፡ “እርስ በእርስም በደንብ ይግባባሉ፡፡”
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኃይሌ ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኀላ በተደጋጋሚ የሚያነሳው ነገር “የብሔራዊ ቡድኑን ስሜት መመለስ” ነው፡፡ የወጣት ቡድኑ አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የላቀ እንደሆነ ሻምበል ቶሎሳ ይናገራሉ፡፡ “አዲስ ትውልድ ናቸው፡፡ በቀላሉ መግባባት ይችላሉ” በማለትም ምክንያቱን ያስረዳሉ፡፡ በ5000ሜ ከሰለሞን ባረጋ ጋር ኢትዮጵያን የሚወክለው ጥላሁን ኃይሌም በአሰልጣኙ ሀሳብ ይስማማል፡፡ “ከብሔራዊ ቡድን ዉጪም ከብዙዎቹ ጋር አብረን ልምምድ እንሰራልን፡፡ ሻይ ቡናም እንላለን” ብሏል ከውድድሩ በፊት በአራራት ሆቴል በሰጠው ቃለ ምልልስ፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ፕሬስ አታሼ ስለሺ ብስራትም “አንድነት እና ጠንካራ የማሸነፍ መንፈስ ያለበት ቡድን ነው” ይላል፡፡

በ “መሰናክል” መጀመር

ብሔራዊ ቡድኑ የታምፐሬ ፈተናውን በከባዱ ፈተና ጀምሯል-በሴቶች 3000ሜ መሰናክል፡፡ በውድድሩ የተሳተፉት ሁለቱም አትሌቶች ወደ ፍፃሜ አልፈዋል፡፡ በምድብ ሶስት የሮጠችው እታለማሁ ስንታየሁ ርቀቱን በ9:52.92 ደቂቃ በመጨረስ የራሷን ምርጥ ሰዓት አሻሽላለች፡፡
በምድብ ሁለት አገሬ በላቸው ለራሷ የዓመቱ ምርጥ ሰዓት በሆነ 9:59.95 በመሮጥ ለነገው ፍፃሜ አልፋለች፡፡

በ1500ሜ ወንዶች ማጣሪያ የኢትዮጵያ ከ20ዓመት በታች ሻምፒዮኑ ብርሃኑ ሶርሳ እና ውድድሩን እንደሚያሸንፍ በብዙዎች ግምት የተሰጠው ርቀቱ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ሻምፒዮን ሳሙኤል ተፈራም ለሀሙሱ ፍፃሜ አልፈዋል፡፡

በ800 ሜትር ሴቶች ፍሬወይኒ ሀይሉ እና የርቀቱ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ውድድር አሸናፊዋ ድርቤ ወልተጂ ከየምድባቸው አንደኛ በመሆን የነገውን ግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያ ይጠብቃሉ፡፡

በ20 ዓመት በታች ሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በምትሳተፍበት የ400ሜ ውድድር በሴቶች ዛሬ በሚደረገው ማጣሪያ የርቀቱ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮኗ ፍሬህይወት ወንዴ እና ማህሌት ፍቅሬ ተሳታፊ ናቸው፡፡

የመጀመሪያዎቹ ፍፃሜዎች

5000ሜ ሴቶች ኢትዮጵያ ሜዳልያ ታገኝባቸዋለች ተብለው ከሚጠበቁት ርቀቶች አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የመጀመሪያው የፍፃሜ ውድድርም ይሆናል፡፡ ድንቅ የውድድር ዘመን እያሳለፈች የምትገኘው ግርማዊት ገብረ እግዚአብሔር ቅድሚያ ግምት አግኝታለች፡፡ ግርማዊት በ35ኛው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ የ6ኪ.ሜ አሸናፊ ስትሆን የአፍሪካ አገር አቋራጭ የርቀቱ ሻምፒዮንም ናት፡፡ በአሰላ በተካሄደው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮናም የ5000ሜ ባለድል ነች፡፡ በአሰላው ውድድር ሁለተኛ የወጣችው እጅጋየሁ ታዬ ሌላኛዋ የ5000ሜ ተፈላሚ ናት፡፡ “እስካሁን የነበረው ዝግጅት በጣም ቆንጆ ነበር፡፡ ወርቅ እናመጣለን ብዬ እየጠበቅኩ ነው” ብላለች እጅጋየሁ፡፡

የወንዶች 10,000ሜ ፍፃሜም ዛሬ የሚደረግ ሲሆን በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ወርቅና ብር ያመጡት በሪሁ አረጋዊ እና ኦሊቃ አዱኛ ይፎካከራሉ፡፡ “ሰርተናል…ተዘጋጅተናል” ያለው በሪሁ” ከኦሊቃ ጋር ተባብረን አሪፍ ሩጫ እንሮጣለን” በማለት ስለዛሬው ፍፃሜ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በታምፐሬ ዶሃን ማለም

ከሁለት ዓመት በፊት በቢድጎሽ- ፖላንድ በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ አራት የወርቅ፡ ሁለት ብር እና አራት ነሃስ ሜዳልያዎችን አሸንፋለች፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ የቴክኒክ መሪ ዱቤ ጅሎ ፌዴሬሽኑ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዳቀደ አስታውቀዋል፡፡ ይህ ውድድር በሚቀጥለው አመት በዶሃ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሰረት እንደሚሆናቸው የተናገሩት አቶ ዱቤ አሁን በወጣት ቡድኑ ውስጥ ከሚገኙት አትሌቶች መካከል “80%ቱ የዓለም ሻምፒዮናው ላይ የሚታዩ” እንደሚሆኑም እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

 

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *