ኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም

ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በውድድሩ የተለመደውን የበላይነታቸውን አሰመስክረዋል

የ2019 ዱባይ ማራቶን አሸናፊዎች

ዱባይ ጥር 17/2011 – ዛሬ ረፋዱን በተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች በተከናወነው የ2019 የዱባይ ማራቶን ውድድር አትሌት ጌታነህ ሞላ 2:03:34 በሆነ ሰዓት የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገውን የማራቶን ውድድር በአሸናፊነት አጠናቋል፡፡

የሀገሩ ልጆች ሄርጳሳ ነጋሳ እና አሰፋ መንግስቱም ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ፡ በእለቱ ወድድር 4ኛ እና 10ኛ  ደረጃን ይዘው ካጠናቀቁት ኬንያዊው ኤማኑኤል ኪፕኬምቦ እና ስዊትዘርላንዳዊው ታደሰ አብረሃም በስተቀር፡ ከ1-10 ያሉ ቀሪ ቦታዎች በሙሉ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ተይዘው ነው የተጠናቀቀው፡፡

ኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቼፒንጌቲች የቦታውን ክብረወሰን እና ከፓውላ ራድክሊፍ እና ሜሪ ኬታኒ በመቀጠል የአለም ሶስተኛውን ፈጣን ሰዓት  በማስመዝገብ  (02:17:08) ስታሸንፍ፡ ኢትዮጵያውያኖቹ ወርቅነሽ ደገፋ እና ወርቅነሽ ኢደሳ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

ጌታነህ ያስመዘገበው ሰዓት የኢትዮጵያ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ሰሆን፡ አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ ያስመዘገበችው 02:17:41 ሰዓት ደግሞ የኢትዮጵያ ሴቶች ማራቶን ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከውድድሩ መጠናቀቅ በሗላ አስተያዬቱን የሰጠው አትሌት ጌታነህ ሞላ” የመጀመሪያ ማራቶኔ እንደመሆኑ መጠን፡ አቅሜን ለማወቅ ነበር የገባሁት፡ አንድ ኪሎ ሜትር እስኪቀረኝ ድረስም እንደማሸንፍ እርግጠኛ አልነበርኩም ” ያለ ሲሆን በቀጣይ የአለም ሻምፒዮናን ታሳቢ፡ በማድረግም በፍጥነት ወደ ትራክ ልምምዱ እንደሚመለስም ገልጿል፡፡ 

አትሌት ወርቅነሽ  ደገፋ በበኩሏ ” በውድድሩ አንደኛ ባለመውጣቴ በፍጹም አልቆጭም ምክንያቱም ያስመዘገብኩት ሰዓት የበለጠ አስደሳች ስለሆነ” ብላለች ወርቅነሽ ከሁለት ወራት በሗላ በሚካሄደው የቦስተን ማራቶን መሳተፍ ቀጣይ እቅዷ እንደሆነም ገልጻለች፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *