ኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም

Ethiopian fans at the Dubai Marathon
photo by: the Organizers

ዱባይ ጥር 17/ 2011 ዓ.ም   – እንዲህ እንደዛሬው በአለም ታዋቂ ከሆኑ ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ተርታ ከመሰለፉ በፊት፡ ውድድሩ አንድ ሁለት እያለ ከሚውተረተርበት ጊዜ ጀምሮ ያውቁታል፣ ከ25 አመታት በላይ ኑሯቸውን በዱባይ ያደረጉት እና ኢትዮያውያን ደጋፊዎችን ከመጀመሪያው የዱባይ ማራቶን ወድድር ጀምሮ እያስተባበሩ የሚገኙት ወ/ሮ ቀለሟ አለማር፤

በውድድሩ የመጀመሪያዎቹ አመታት የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱም፣ ተሳታፊ የሆኑ አትሌቶች ብቻ ሳይሆን ውድድሩ መኖሩን አውቀው ለማበረታት እና ለመታደም የሚሄዱ ደጋፊዎች ቁጥርም እስከዚህም እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን በቀድሞ ጊዜ አትሌት የነበሩት የውድድሩ መስራች አህመድ አልካማሊ፡ ኢትዮጵያውያን ለስፖርቱ ያላቸውን ፍቅር በሚገባ ይረዱ ስለነበር፡ በዱባይ እና በአካባቢው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መንገድ ጥሪ ማስተላለፍ ይጀምራሉ፣ ቀስ በቀስም የኢትዮጵያን አትሌቶች እና ደጋፊዎች ተሳትፎ እየጨመረ መጥቶ፡ በዚህ ሰአት ውድድሩን በሩጫውም ሆነ በድጋፉ ያለ ኢትዮጵያውን ማሰብ እስከማይቻልበት ደረጃ ሊደርስ እንደቻለ ይናገራሉ፡፡

በተለይም ደግሞ ከአስራ ሁለት አመታት በፊት የአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ እና ለተከታታይ ጊዜያት ድል ማድረግ ኢትዮጵያውያንን አና ውድድሩን የበለጠ እንዲተሳሰሩ ያደረገ ሁነት እንደሆነ አዘጋጆቹም ሆነ ወ/ሮ ቀለሟን እና አቶ ሙሉጌታ ጠብቀውን ጨምሮ ሌሎች በዱባይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ልብ የሚስማሙበት ሃሳብ ነው፣ እንዲያውም ከቅርብ ጊዘያት ወዲህ የውድድሩ አዘጋጆች ኢትዮጵያውያንን ደጋፊዎች የውድድሩ ድምቀት መሆንን በሚገባ በመረዳት፡ ከዱባይ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ጋር በመተባባር አንዳንድ ደጋፊዎችን የማስተባበር ስራዎች ላይ እገዛ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ: በዱባይ ማራቶን የኢትዮጵያውን አትሌቶች በተከታታይ ውጤታማ መሆን በዱባይ እና በአካባቢው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውን እያበረከተ የሚገኘውን በጎ ነገር ሲገልፁ  “ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵውያን ቀኑን ሙሉ በተለየዩ የሀገሬው የብዙሀን መገናኛዎች በጎ በጎውን የምንሰማበት፣ በስራ ብዛት ምክንያት ዓመቱን ሙሉ የማናገኛቸውን ሰዎች የምንገናኝበት እና ሀገር ቤት የገባን ያክል የምንደሰትብት ልዩ የሆነ የበዓል ስሜት የምናገኝበት እለት ነው” ሲሉ ወ/ሮ ቀለሟ በበኩላቸው  “በስደት፡ በሰው ሀገር መሆናችን ረስትን በደስታ የምናከብረው፣ በመጥፎ የሚነሳው ስማችን ቀርቶ  ስለአሸናፊነታችን ሲወራ የሚውልበት እና የመሰባሰቢያችን ምክንያት ነው” በማለት ይገልጹታል፡፡

በውድድርም ሆነ ከውድድር ውጭ ኢትዮጵያውያን ጎልተው የሚታዩበት የዱባይ ማራቶን 20ኛው ውድድር በዛሬው እለት ከጠዋቱ 11፡00 ጀምሮ ይከናወናል፣ እስካሁን ከተካሄዱት 19 ውድድሮች መካከል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፡ በወንዶች 12 ጊዜ፡ በሴቶች ደግሞ ለ14 ጊዜያት አሸናፊዎች መሆን ችለዋል፣  ይህንን ውጤታማነት ለማስቀጠል እና የውድድሩ ድምቀት ለመሆን አትሌቶቻችንም ሆነ ደጋፊዎቻችን ዝግጅታቸውን አጠናቀው  የውድድሩን መጀመሪያ በመጠባባቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

Please follow and like us:

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *